የኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባቱን የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማሳወቃቸውን ተከትሎ በአገራችን በተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት በርካታ ወገኖቻች ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ ናቸው፡፡ ቫይረሱ በህብረተሱ ጤና እና ገቢ ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ መንግስትም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ አዋሽ ባንክም የመንግስትን እርምጃ በመደገፍ ለአገር አቀፍ እርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ የአስር ሚሊዮን ብር ድጋፍ ያበረከተ ሲሆን፣የሚያግዟቸው ደጋፊ ወላጆች ለሌላቸው ተማሪዎች የመመገቢያ ድጋፍ ይሆን ዘንድም በፋሚሊ መርሲ ሀውስ በኩል የአንድ መቶ ሺህ ብር እርዳታ አድርጓል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ መንግስት እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ከመደገፍ ባሻገርም በመዲናችን በተለያዩ አካባቢዎች በወረርሽኙ ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እንቅስቃሴአቸው በመገደቡ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንም ለመርዳት ከተለያዩ አካላት ጋር በመስራት ላይ የሚገኘው አዋሽ ባንክ፣ እነሆ ዛሬም ከበድር ፋውንዴሽን ጋር በመተባበበር በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ 06 በኮሮና ቫይረሽ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ህብረተሰብ ከፍሎች የብር 500 ሺህ ልገሳ አድርጓል፡፡ በዚህም ልገሳ ለ250 አባወራዎች የአንድ ወር ቀለብ መግዣ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡
በስፍራው በመገኘት ለተረጂዎች ዕርዳታውን የሰጡት የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው ባደረጉት ንግግር አብሮን በኖረው የመደጋገፍ አኩሪ ኢትዮጵያዊ ባህላችን ይህንንም ጊዜ እናልፋልን የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸው ገልጸው ይህንን ችግር አስሰከምንሻገር ድረስ ባንኩ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አዋሽ ባንክ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ እና ቫይረሱ በባንኩ ደንበኞች፣ ሰራተኞች እና መላው ህብረተሰብ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከዚህ በፊት የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆቱ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡-
- የመተማመኛ ሰነድ (Letter of Credit) ማራዘሚያ ላይ የሚከፈለው ክፍያ እንዲቀር ተደርጓል
- የብድር ማራዘሚያ ላይ የሚከፈለው ክፍያ እንዲቀር ተደርጓል፡፡
- መላው የባንኩ ሰራተኞች እና የባንኩ ደንበኞች በበሽታው እንዳይጠቁ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ከማስገንዘቡም በላይ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል
- የባንካችን ደንበኞችን እና መላው ህብረተሰባችን በባንካችን ቅርንጫፎች ሲገለገሉ ላልተገባ መጨናነቆች/መቀራረቦች/እንዳይጋለጡ የባንካችንን የሞባይል ባንኪንግ፣ የኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ኤቲኤም እና ፖስ ማሽኖችን ከሌላው ጊዜ በተሸለ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ለማበረታታት ሲባል ይከፈሉ የነበሩ የአገልግሎት ክፍያዎችን እ.አ.አ ከኤፕሪል 01/2020 ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ወራት በተለይም በATM ወጪ ላይ ይከፈል የነበረውን ኮሚሽን ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ እና
- የችግሩ ቀጥተኛ ተፅእኖ ሰለባ ለሆኑት አገልግሎት ሰጪ ሴክተሮች ላይ ለተሳማሩት ተበዳሪ ደንበኞቹ ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ቅነሳ ማድረጉ በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡