አዋሽ ባንክ እ.አ.አ. የ2018/19 የመጀመርያ ግማሽ ዓመት የዕቅድ ክንውኑን ገመገመ

አዋሽ ባንክ  የመሪነት ደረጃው ለአራተኛ ጊዜ አረጋገጠ

አዋሽ ባንክ በዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ከግል ባንኮች መካከል የነበረውን የመሪነት ስፍራ ዘንድሮም ለአራተኛ ዓመት በመድገም ላይ  እንደሚገኝ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡

የባንኩ ስራ አመራሮች በተገኙበት ጥር 20/2011 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በተካሄደው ግመገማ ላይ፣

  • ባንኩ የመሪነቱን ደረጃ ዘንድሮም ለአራተኛ ጊዜ ማረጋገጡ
  • የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳብ 52.4 ቢሊዮን ብር መድረሱ
  • የባንኩን ራዕይና ግብ ለማሳካት በአዋሽ ባንክና በትላልቅ ባንኮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብና  ከተወዳዳሪዎቹ  ደግሞ ቀድሞ ለመገኘት የሁሉም ባለድሻ አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ  በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት (እ.አ.አ.2018/19) የስራ አፈፃፀም ግምገማ ጥር 20/2011 ሲካሄድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለፁት  ባንኩ ካስቀመጠው እቅድ አኳያ፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር እና ከሌሎች የግል ባንኮች አፈፃፃም አኳያ ሲታይ እጅግ አስደሳች ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ይህም ባንኩ በዋና ዋና የሥራ ዘርፎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ከግል ባንኮች መካከል የነበረውን የመሪነት ስፍራ ዘንድሮም ለአራተኛ ዓመት በመድገም ላይ መገኘቱን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

ባለፉት ስድት ወራት ባንኩ አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት ባደረገው  የተቀናጀ እንቅስቃሴ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ትላልቅ ደንበኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና በርካታ ግለሰቦችን የባንካችን ደንበኞች ለማድረግ ተችሏል፡፡ ለደንበኞቻችን የምንሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻልና ፍላጐታቸውን ለማርካትም የተለያዩ ስራዎች ተሠርተዋል፡፡

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የደንበኞቻችንን ጊዜና ወጭ ቆጣቢ የሆኑ የባንክ አገልግሎቶች በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ለአብነትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትኬቶችን ፣ የዲኤስቲቪ እና  የትምህርት ቤት ክፍያዎችን፣ እንዲሁም  የኢትዮ-ቴሌኮም ካርድ ግዥዎችን በሞባይል ባንኪንግ በመጠቀም ክፍያ መክፈል የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡በተመሳሳይ መልኩ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችም በሥራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መኆኑን ገልፀው  ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሥራ ላይ በዋለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትም በአሁኑ ጊዜ በ311 ቅርንጫፎች አገልግሎቱ እየተሰጠ መሆኑንና በዚህም እ.ኤ.አ ዲሴምበር 2018 መጨረሻ ላይ ከብር 1.3 ቢሊዮን በላይ የተቀማጭ ሂሳብ ለመሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

 

የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳብ 52.4 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም አሀዝ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ የብር 16.4 ቢሊዮን ወይም የ46 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ለግማሽ ዓመቱ ከተቀመጠው ዕቅድ አኳያ ግን የብር 416.2 ሚሊዮን ወይም የ1 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ሌሎች የግል ባንኮች ካስመዘገቡት እድገት አኳያም የአዋሽ ባንክ ዕድገት  በመጠኑ ከፍተኛው ነው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን የብር 11 ቢሊዮን ወይም 42 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ብር 37.2 ቢሊዮን ሆኗል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከተቀመጠለት እቅድ አኳያ ደግሞ የብር 565 ሚሊዮን ወይም የ2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አስተረድተዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ አዋሽ ባንክ ከግል ባንኮች ሁሉ ቀዳሚውን ሥፍራ እንደያዘ ቀጥሏልም ብለዋል፡፡

በሌላ መልኩ የአንድ ባንክ ብድር ጤነኛነት የሚለካው በተበላሹ ብድሮች ምጣኔ እንደመሆኑ መጠን በዚህም መሠረት ምንም እንኳን የባንኩ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ አምና ከነበረበት 3.3 በመቶ ወደ 2.9 በመቶ ዝቅቢልም በቀሩት ወራት ውስጥ የተበላሹ ብድሮችን ባንኩ ካስቀመጠው የ2 በመቶ ግብ አኳያ ለማሳካት ሁሉም የሪጂናልና የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች ከዋናው መ/ቤት አካላት ጋር ተቀናጅተው የተጠናከረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል ፡፡

በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ውስጥ ባንኩ ከተለያዩ ምንጮች ያገኘው ገቢ ብር 3.6 ቢሊዮን ሲሆን ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት እና ከእቅዱ አኳያ በተከታታይ የ53 በመቶ እና የ2 በመቶ ብልጫ ቢያሳይም የባንካችን ጠቅላላ ወጪ የብር 681.5 ሚሊዮን ወይም የ40 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ብር 2.4 ቢሊዮን ደርሷል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ለወጪዎቹ ማሻቀብ ዋና ዋና ምክንያቶች የወለድ ክፍያ በብር 355 ሚሊዮን እና፣ የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅም ደግሞ የብር 188.8 ሚሊዮን ጭማሪ ማሳየት መሆኑን አብራርተው የወጪ አወጣጣችን ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እና የሠራተኛውን ምርታማነት ማሳደግ ላይ ሁላችንም ተረባርበን መስራት  እንዳለብን አመላካች ነውም ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡

ምንም እንኳን እነዚህና ሌሎች ተግዳሮቶች ቢያጋጥሙትም እ.ኤ.አ ዲሴምበር 2018 ላይ የባንኩ ያልተጣራ ትርፍ ብር 1.14 ቢሊዮን ሆኗል፡፡ ይህም ትርፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ሲታይ የብር 549 ሚሊዮን ወይም የ92 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡ይህም እድገት በባንካችን ታሪክም ሆነ በሌሎች የግል ባንኮች ዘንድ ያልተመዘገበ  ውጤት ነው ብለዋል ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ፀሐይ  ሽፈራው፡፡

 

 

 

Share
Facebook
Twitter
LinkedIn
Telegram

Oct 10, 2024 EXCHANGE Rate
Currency Buying Selling
USD
111.4816 125.8886
GBP
144.6929 154.7637
EUR
123.9777 136.5008
AED
30.6012 31.0175
SAR
29.9606 30.3682
CHF
127.9601 136.8664

Exchange Rate
Close