የአዋሽ ባንክ የስራ አመራሮች እ.ኤ.አ የ2018/19 የሂሳብ ዓመት የስራ አፈፃፀም እና የ2019/20 የስራ ዕቅድ እና በጀት ላይ ተወያዩ፡፡

በስበሰባው ላይ ባንኩ እ.ኤ.አ በ2018/19 ላስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፀሐይ ሽፈራው ሁሉንም ባለድርሻ አካለት በማመስገን ለቀጣይ በጀት ዓመትም ለላቀ ውጤት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ የዋና ስራ አስፈፃሚው ሙሉ መልዕክትም እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የ2018/19 ሂሳብ ዓመት የባንካችን የስራ አፈፃፀም እንደሚያሳየው ባንካችን በዋና ዋና የስራ ዘርፎች ማለትም በተቀማጭ ሂሳብ፣ በብድር፣ በጠቅላላ ሀብት፣ በተከፈለ ካፒታል እና በትርፍ ከግል ባንኮች የቀዳሚነት ስፍራውን የያዘ ሲሆን የመሪነት ደረጃውን መሰረቱ በማይናወጥ ዓለት ላይ ከመገንባትም አልፎ በአገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሚባለውን ትርፍ በማስመዝገብ ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር ያለውን ልዩነት በማስፋት መሪነቱን ለአራተኛ ጊዜ አረጋግጧል፡፡ ለዚህ አመርቂ ውጤት መብቃት የቻልነው በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በሳልና ብልህ አመራር፣ በማኔጅመንቱ የዕለት ተዕለት የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ እንዲሁም በየደረጃው ባሉት ሠራተኞች ትጋት በመሆኑ ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን እላለሁ፡፡
እ.ኤ.አ በ2018/19 የሂሳብ ዓመት ባንካችን በርካታ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን ለዚህ ስብሰባ ውይይት እንደ መነሻ ሃሳብ የሚያገለግሉትን ዋና ዋና ተግባራት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡-
1.ባንካችንን ከአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ካሉት አስር ምርጥ ባንኮች ተርታ ለማሰለፍ ከተዘጋጀው የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ (Vision 2025) አኳያ ሁሉም የባንካችን የሥራ ክፍሎች የ2018/19 የስራ ዕቅዶችን እንዲያዘጋጁና ተግባር ላይ እንዲያውሉት የተደረገ ሲሆን አፈፃፀሙም በየጊዜው እየተገመገመ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተደርጓል፡፡ እስከ አሁን ባለው የአፈፃፀም ሂደትም ባንካችን ራዕዩን ማሳካት ብቻ ሳይሆን ከዚያ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚችል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
2.የባንካችን ሪሶርስ ሞቢላይዜሽን ኮሚቴ እና በየቅርንጫፎቹ የተቋቋሙት ንዑሳን ኮሚቴዎች ከቀጠና ስራ አስኪያጆች እና ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የባንካችን ተቀማጭ ሂሳብ ዕድገት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት በባንካችን ታሪክ ብቻ ሳይሆን በግል ባንኮች ታሪክም የመጀመሪያው የሆነውን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በተለይም ትላልቅ ደንበኞች፣ላኪዎች እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) የባንካችን ደንበኞች እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ከዚህ የተቀናጀ ጥረታችን የተነሳ ጠቅላላ የባንካችን የውጭ ምንዛሪ ግኝት እ.ኤ አ በ2017/18 ከነበረበት 598.3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የ53 በመቶ ዕድገት በማስመዘገብ 917.4 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሆኗል፡፡ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳብ የ16.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ36 በመቶ ዕድገት በማሳየት ብር 62.2 ቢሊዮን ሆኗል፡፡የባንኩ አስቀማጮች ቁጥርም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡በዚሁ አጋጣሚ ለዚህ ለተገኘ ውጤት ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ቅርንጫፎች በተለይም በዋናው መ/ቤት ደረጃና በተለያዩ እርከን ላይ የሚገኙ የሪሶርስ ሞቢላይዜሽን ኮሚቴ አባላት ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ አሁን የተገኘው ውጤት 20 በመቶ የማይበልጡ ቅርንጫፎች ከዕቅዳቸው በላይ ባስመዘገቧቸው ውጤት ስለሆነ በሚቀጥለው ዓመት በእነዚህ ቅርንጫፎችና ስራ ክፍሎች ላይ ብቻ መንጠልጠል ቀርቶ ሁሉም ቅርንጫፎች በቻሉት መጠን የራሳቸውን አስተዋፅኦ በትልቁ እንዲወጡና ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለመውሰድ ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
3.ደንበኞቻችን ከባንካችን ጋር ሲሰሩ ምልልስና እንግልት እንዳይገጥማቸው ጉዳያቸው በሚመለከተው አካል በፍጥነት ታይቶ መፍትሔ እንዲያገኝ የሆልሴል እና የሪቴይል የስራ ክፍሎች በበቂ የሪሌሽንሺፕ ማናጀሮች እንዲደራጁ በመደረጉ ደንበኞቻችን በተመደቡላቸው የሪሌሽንሺፕ ማኔጀሮች አማካኝነት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡ከዚህም በተጨማሪ፡-
•በተለመደው የባንክ አሰራር በወለድ ማስቀመጥና በወለድ መበደር የማይፈልጉ ወገኖቻችን ፍላጎት ለማርካትም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ( Interest Free Banking) በተሻለ ደረጃ ለመስጠት ከፍተኛ ስራዎች በዓመቱ ተሰርተዋል፡፡ አበረታች ውጤትም ተመዝግቧል፡፡ በዚህ ዘርፍ ከ131 ሺ በላይ ደንበኞችን ማፍራት የተቻለ ሲሆን ከብር 2.2 ቢሊዮን በላይ ተቀማጭ ሂሳብ መሰብሰብም ተችሏል፡፡
•የቅርንጫፎቻችንን ችግር በቅርበት ለመገንዘብና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የባንኩ የበላይ አመራርና ማኔጅመንት አባላት በቡድን ተከፋፍለው ብዙዎቹን ቅርንጫፎች እንዲጎበኙ ተደርጓል፡፡ በጉብኝት ወቅት የተስተዋሉ ችግሮችም በየደረጃው በሚመለከተው አካል የማስተካከያ እና የመፍትሔ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ተደርጓል፡፡
•የባንካችንን ተደራሽነት ለማስፋትና ህብረተሰባችን የባንክ አገልግሎት በአቅራቢያው እንዲያገኝ ለማስቻል እ.ኤ.አ በ2018/19 የሂሳብ ዓመት 40 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ለመክፈት አቅደን 44 ቅርንጫፎችን ከፍተን ለአገልግሎት አብቅተናል፡፡ በመሆኑም በሂሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ በ410 ቅርንጫፎች ለህብረተሰባችን የተሟላ አገለግሎት እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን በሳምንት 7 ቀናት እና በቀን 24 ሰዓት አገልግሎት በሚሰጡ 270 ATM ማሽኖች፣ ከ500 በላይ በሚሆኑ POS ማሽኖች፣ እንዲሁም 27 ያህል በሚሆኑ ወኪሎች በመታገዝ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡
•የATM ማሽን አገልግሎት ለሁሉም ቅርንጫፎቻችን ለማዳረስ ሲባልም በአሁኑ ወቅት 200 ተጨማሪ የ ATM ማሽኖችን በመግዛት እያሰራጨን ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሞላ ጎደል ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ቅርንጫፎቻችን የ ATM ማሽኖች ይኖራቸዋል፡፡ የአንድ ሺህ ተጨማሪ POS ማሽኖች ግዥም ተፈፅሟል፡፡ ይህም ለደንበኞች አገልግሎታችንን የበለጠ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደንበኞቻችን ባሉበት ቦታ ሆነው ተገቢውን የባንክ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችላቸውን የሞባይል ባንኪንግ እና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶችን በስራ ላይ ያዋለ ሲሆን እ.ኤ.አ ሰኔ 2019 መጨረሻ ላይ ከ370 ሺህ በላይ የሚሆኑ ደንበኞች የM-Wallet እና ከ 33 ሺህ በላይ ደንበኞች የኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
•ደንበኞቻችን በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ አስተያየት ለመስጠት እንዲችሉና ማንኛውንም ማብራሪያ ጠይቀው እንዲረዱ ለማስቻልም የደንበኞች ግንኙነት ማዕከልን (Contact Center) የበለጠ ለማዘመን ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ ነው፤ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ በስራ ላይ የሚውል ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአገራችን በግል ባንኮች ታሪክ ስራ ላይ ያልዋለውን የደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር የ(Customer Relationship Management) በባንካችን ውስጥ አገልግሎት ላይ ለማዋል የመጨረሻ ምእራፍ ላይ እንገኛለን፡፡
ከ2017/18 ሂሳብ ዓመት ጀምሮ የባንካችን የሂሳብ አያያዝ እና ሪፖርት አሰራር በIFRS መስፈርቶች መሠረት መሆኑ ይታወሳል፡፡ከዚሁ ጋር በተያያዘ የባንካችንን ሪፖርት እ.ኤ.አ ከ2018/19 ጀምሮ በIFRS 9 (ዘጠኝ) መሠረት ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው በጀት ዓመት የባንካችንን መልካም ስምና ገፅታ ለማጎልበትም አዳዲስ የተከፈቱ ቅርንጫፎቻችን በሙሉ የውስጥ አደረጃጀታቸው እና አርማ በአዲሱ አሰራር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የዋናው መ/ቤትና የተመረጡ ቅርንጫፎቻችንን በአዲስ የውስጥ አደረጃጀት (Interior Design) ለማስዋብ የተጀመረው ጥረት ግን በሚፈለገው ፍጥነት ሊሄድልን አልቻለም፡፡
ባንካችን ከሚታወቅበት ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ በተለያዩ የሀገሪቷ ዋና ዋና ከተሞች ሕንጻዎችን በመገንባት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ባንካችን ከግል ባንኮች የራሱን የዋና መ/ቤት ሕንጻ በማሠራት የመጀመሪያው የግል ባንክ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪም ባንካችን ባለፉት ዓመታት የራሱን ሕንጻዎች በመገንባትም ሆነ የተገነቡትን በመግዛት ተምሳሌት የሆነ ባንክ ነው፡፡ ባሳለፍነው በጀት ዓመትም ባለ ስድስት ፎቅ የጅማ ከተማ ህንፃችን ግንባታ እየተጠናቀቀ ሲሆን በመጪው መስከረም ተመርቆ ስራ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል በባሌ ሮቤ ለሚገነባው ባለ አራት ወለል እና አንድ ምድር ቤት አዲስ ህንፃም የግንባታ ጨረታው ወጥቶ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡
የባንካችንን የዋና መ/ቤት ዘመናዊ ሕንፃ (Complex Building) ለመገንባት እና የ Training Institute Center ለማቋቋም የቦታ ጥያቄ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበን በጎ ምላሻቸውን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ ለወደፊቱም አዋሽ ባንክን የሚመጥንና የባንካችንን ስም ሊያስጠራ የሚችል የተሻለ ዋና መ/ቤት ለመስራት ለሚመለከተው የመንግስት አካል ላቀረብነው ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቦታውን እናገኛለን ብለን እናስባለን፡፡
አጠቃላይ የባንኩን የፋይናንስ አፈፃፀም በተመለከተም የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሂሳብ ኤልሲ ማርጅንን ጨምሮ እ. ኤ. አ 2018/19 ሂሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከብር ከ62.2 ቢሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ ይህም ካለፈው የሂሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ16.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ36 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በሂሳብ ዓመቱ ውስጥ ባንካችን ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው የብድር መጠን (Outstanding loan) ከብር 47.1 ቢሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ይህም ባለፈው የሂሳብ ዓመት ከነበረው የብር 31.3 ቢሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ51 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የባንኩ ብድር 51 በመቶ ማደግ ለዚህ ዓመት ትርፋማነት ወሳኝ ስለሆነ ለወደፊቱም የብድር መጠንን (Loan Portifolio) ለማሳደግና የባንካችንን ትርፋማነት ዕድገት አስጠብቀን ለመጓዝ የተቀማጭ ሂሳብ ዕድገት ላይ መስራት አማራጭ የሌለው ስትራቴጂ መሆኑን ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል፡፡
በሌላ መልኩ በ2018/19 የሂሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንከችን የተበላሹ ብድሮች መጠን የብር 91.7 ሚሊዮን ጭማሪ በማሳት ወደ ብር 540.9 ሚሊዮን ብር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ብድር ጥምርታ አኳያ ግን ባለፈው ዓመት ከነበረው 1.4 በመቶ ወደ 1.15 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም ባንካችን ካስቀመጠው የ2 በመቶ እቅድና ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የ5 በመቶ ምጣኔ አኳያ የባንካችን የብድር ጤንነት ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡ ነገር ግን ይህን አነስተኛ የተበላሹ ብድሮች ምጣኔ በ2019/20 ሂሳብ ዓመትም ለማስቀጠል ከወዲሁ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል፡፡
ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ባንካችን ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ወደ ስምንት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ አግኝቷል፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት ከተገኘው ገቢ የብር 2.6 ቢሊዮን ብልጫ ወይም የ47 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከጠቅላላው ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ማለትም 74 በመቶ የያዘው ከወለድ የተገኘ ገቢ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ገቢያችን በወለድ ላይ ከፍተኛ ጥገኛ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ለወደፊቱ ሌሎች የገቢ ምንጮችን ለማስፋት ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንዳለብን አመላካች ነው፡፡ በሌላ መልኩ የባንካችን ጠቅላላ ወጪ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የብር 1.5 ቢሊዮን ወይም የ43 በመቶ ዕድገት በማሳየት ብር 4.9 ቢሊዮን ሆኗል፡፡
ለወጪዎቹ መናር ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ያበረከቱት እንደተለመደው በተቀማጭ ሂሳብ ላይ የሚከፈለው የወለድ ምጣኔ በ42 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ እና የሰራተኞች ደመወዝና የጥቅማጥቅም ወጪ የብር 379.1 ሚሊዮን ዕድገት በማሳየት ወደ ብር 1.6 ቢሊዮን ከፍ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን የደመወዝና የጥቅማጥቅም ወጪ ወደ 1.6 ቢሊዮን ከፍ ቢልም ባንካችንም የተሻለ ትርፍ እያስመዘገበ ስለሆነ የባንኩ ሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማጥቅም እያደገ መሄድ እንዳለበት እናምናለን፡፡ በመሆኑም ባንኩ ለሰራተኞቹ እያወጣ ያለውን ከፍተኛ ወጪ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሁሉም የባንኩ የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች የእኔነት ስሜት ተሰምቶን የባንካችንን ምርታማነት እንድናሳድግና የወጪ ቁጠባ ባህላችንን ከምንጊዜውም በላይ እንድናጠናክር ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት የባንካችን ያልተጣራ ትርፍ ብር 3.3 ቢሊዮን ሆኗል፡፡ ይህም ትርፍ በአንድ ዓመት ብቻ የ1.36 ቢሊዮን ብር ወይም የ70 በመቶ ዕድገት የታየበት በመሆኑ በአገራችን የግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያውን ስፍራ ይይዛል፡፡
በአጠቃላይ የባንካችን የ2018/19 የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ባንካችንን ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ካሉት ምርጥ አስር ባንኮች ተርታ ለማሰለፍ በ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ ላይ ያስቀመጥነውን ግብ ለማሳካት በሚያስችለን ቁመና ላይ እንደምንገኝ አመላካች ነው፡፡ በመሆኑም በተገኘው ውጤት ሳንኩራራ በሚቀጥሉት ዓመታት በተለመደው የአዋሽ ባንክ ባህል እንደ አንድ አካል ሆነን እጅ ለእጅ ተያይዘን የመጨረሻውን ግባችንን ለማሳካት በአንድነት መንፈስ እንድንሰራ ከአደራ ጭምር ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ የተገኘው ውጤት በማንኛውም መስፈርት የተሻለና የሚያኮራ ቢሆንም አሁን ሊስተካከሉና ሊሰሩ የሚገቡ ብዙ ስራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል፡፡ ስለዚህ አሁንም አዳዲስ ደንበኞችን ወደ አዋሽ ማምጣትና የባንኩን የገበያ ድርሻ ማሳደግ ላይ በሰፊው ልንሰራ ይገባል፡፡ በብዙ ቅርንጫፎች ትኩረት ያልተሰጠው የደንበኞች መስተንግዶ አሁንም ብዙ የሚቀረው ስለሆነ ቅርንጫፍ ስራአስኪያጆች፣ የቀጠና ስራአስኪያጆችና የዋና መ/ቤት የሚመለከታችሁ ክፍሎች በጋራ መስራት ይጠበቅባችኋል፡፤
የ2019/20 የትኩረት አቅጣጫዎች
ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት የ2019/20 ሂሳብ ዓመት ለአገሪቱም ሆነ ለባንካችን በአጠቃላይ የተለያዩ መልካም አጋጣሚዎች (opportunities) እና ተግዳሮቶች (Challenges/ threat) ከፊትለፊታችን የተደቀኑበት ጊዜያቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ውስጣዊ ጥንካሬያችንን የበለጠ አጎልብተን፣ ያሉብንን ድክመቶች ደግሞ በጊዜው አስተካክለን፣ የተፈጠሩልንን መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም የባንካችንን ውጤታማነትና መልካም ስምና ገፅታ ማስቀጠል የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በሁላችንም እጅ ላይ የወደቀ አደራ ነው፡፡ ይህንንም ታሪካዊ አደራ በብቃትና በውጤታማነት ለመወጣት ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ይጠበቅብናል፡፤ ዋና ዋናዎቹንም እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡-
1.ባንካችን እያሳየ ካለው ፈጣን ዕድገትና በባንኮች መካከል እየተደረገ ያለውን እልህ አስጨራሽ ውድድር ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ፣የባንካችን የውስጥ አደረጃጀት ( Organizational Structure) እንደገና ተፈትሾ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ይደረጋል፡፡ ይህም የማስተካከያ እርምጃ ባንካችን ከተፎካካሪ ባንኮች አንፃር እና ለወደፊቱ ከሚቋቋሙት አዳዲስ ባንኮች አኳያ ሊገጥሙት የሚችሉትን ፈተናዎች መቋቋም የሚያስችለው ቁመና እንዲኖረው ያስችለዋል፡፡
2.የዋናው መ/ቤት የስራ ክፍሎች፣ የሪጅናል ፅ/ቤት እና የባንካችን ቅርንጫፎች ሁሉ እ.ኤ.አ. ለ2019/20 ሂሳብ ዓመት የተቀመጠላቸውን ግብ እንዲያሳኩ ልዩ ክትትልና እገዛ ይደረግላቸዋል፡፡ከዚህ አኳያ በዋናው መ/ቤት፣ በቀጠና ጽ/ቤቶች እና በቅርንጫፎች መካከል ያለውን መስተጋብር በደንብ በማሳለጥ ስራዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ ይደረጋል፡፡
3.የወደፊቱ የባንካችን የመወዳደሪያ ሜዳ Digital Banking ስለሆነና መንግስትም የተለያዩ የ Fintec ካምፓኒዎች ወደ ገበያው እንዲቀላቀሉ ህግ እያረቀቀ ስለሆነ ባንካችን በ Mobile እና Online banking በኩል ያለውን ስራ በዘርፉ በተለያዩ አገርች ልምድ ካላቸው ካምፓኒዎች ጋር በሽርክና ለመስራት በአዲስ መልክ ወደ ገበያው ይገባል፡፡ይህም ሽርክና በትክክል ስራ ላይ ከዋለ አዋሽን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ የሚያሸጋግረውና የባንኩን የገበያ ድርሻ በተሻለ ሊያሳድግ የሚችል አካሄድ ስለሆነ በዚህ በኩል የባንኩ ማኔጅመንት አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡
4.ሁሌም እንደምንገልጸው የተቀማጭ ሂሳብ እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለባንክ ስራ ዋና የጀርባ አጥንት ናቸው፡፡ በመሆኑም ከዚህ በፊት ስናደርግ እንደነበረው ሁሉ የባንካችንን ተቀማጭ ሂሳብ እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማጎልበት አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ነድፈን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አንፃር የሪሶርስ ሞቢላይዜሽን ኮሚቴ ያዘጋጀውን እና ማኔጅመንቱ ስራ ላይ እንዲውል ያጸደቀውን አዲሱን ስትራቴጂ በስራ ላይ ማዋል ይጠበቅብናል፡፡
5.ባሳለፍነው በጀት ዓመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ስራዎች በዘንድሮው በጀት ዓመት እንዲጠናቀቁ ይደረጋል፡፡ ለአብነት ለመጥቀስ ያክልም፡-
የሠራተኞቻችን የስራ ምዘና እና ጥቅማጥቅም አሰጣጥ ስርዓትን የሚያሻሽለው የPerformance Management System እና የሠራተኞቻችንን የስራ ባህልና ምርታማነት የሚያሻሽለው የCultural Transformation ጥናት፣
የደንበኞቻችንን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እና ለደንበኞቻችን ቅሬታ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ መፍትሔ ለመስጠት ታስቦ በሂደት ላይ ያለው የ Contact Center እና Customer Relationship Management Solution ስራዎች፣ እና
የባንካችንን የኮር ባንኪንግ አሰራር ወደ ተሻለ ደረጃ ማሻሻልና ሌሎች በIT በኩል የተያዙ ስራዎች በጊዜ መጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡
6.በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በአገራችንም ጭምር እየተካሄዱ ያሉትን የፖሊሲ ማሻሻያዎች እና ለውጦች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የባንካችን የቪዥን 2025 ስትራቴጂ የእሰካሁኑ ትግበራ ተገምግሞ አዳዲስ ስትራቴጂዎች እንዲዘጋጁ ይደረጋል፡፡
በመጨረሻም እ.ኤ.አ በ2018/19 ሂሳብ ዓመት ባንካችን የተለያዩ ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር አመርቂና አበረታች ውጤት ያስመዘገበበት ዓመት ነው፡፡ ባንካችንን ለዚህ አኩሪ ውጤት ያበቃችሁትን የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች በሙሉ በድጋሚ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
በያዝነው በጀት ዓመትም ባገኘነው ውጤት ሳንኩራራ እና ሳንዘናጋ ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እና ባንካችንን በመሪነት ደረጃ ላይ ለማስቀጠልና በህብረተሰቡ ውስጥ ያገኘውን መልካም ስም በመጠቀም ባንካችንን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በዛሬውና በነገው ዕለት በምናካሂደው ውይይት ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግና በተስብሳቢዎቹ የተደረሰበትን ዋና ዋና ውሳኔዎች በየስራ ክፍላችሁ ስር የሚገኙትን ሰራተኞች በማወያየት የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ፡፡
ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ!!

Share
Facebook
Twitter
LinkedIn
Telegram

May 20, 2024 EXCHANGE Rate
Currency Buying Selling
USD
56.9985 58.1385
GBP
68.8367 70.2134
EUR
61.7864 63.0221
AED
14.0421 14.3229
SAR
13.7538 14.0289
CHF
59.8369 61.0336

Exchange Rate
Close