በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፉ እና ዘመኑን የዋጁ የባንክ አገልግሎቶችን በመስጠት ተደራሽነቱን በማስፋት ላይ የሚገኘው አዋሽ ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር አዲስ አለም አቀፍ ቅድመ-ክፍያ ካርድና የክፍያ ጌትዌይ አገልግሎት ቴክኖሎጂን በዛሬው ዕለት በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በተደረገው የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ይፋ አድርጓል፡፡
የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የባንኩ ሲኒየር ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ ዮሐንስ መርጋ በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት በዛሬው ዕለት ተመርቆ ሥራ ላይ የሚውለው የአዋሽ ዓለም አቀፍ ቅድመ-ክፍያ ካርድ (Awash International Prepaid Card) የባንኩ ደንበኞች በፕላስቲክ ካርዱ አማካይነት እንዲሁም ኤቲኤምን በመጠቀም ገንዘብ ወጪ እንዲያደርጉ ከማስቻሉም በላይ በፖስ ማሽን ክፍያ እንዲፈጽሙና በኦንላይን ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ግብይት መፈጸም እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡