ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ዘመናዊ እና አስተማማኝ የባንክ አገልግሎት ለደንበኞቹ በማቅረብ ከበርካታ የግል፣ የመንግስትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አብሮ እየሰራ የሚገኘው አዋሽ ባንክ ከM-PESA ETHIOPIA ጋር በዲጂታል ቁጠባ እና ብድር አገልግሎት ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የስታራቴጂክ ፓርትነርሺፕ ውል ተፈራርሟል።
የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በዛሬው ዕለት ባንኩ ከM-PESA ETHIOPIA ጋር በተደረገው “እርፍ በኤምፔሳ” የተሰኘው ዲጂታል overdraft የብድር አገልግሎት መተግበሪያ ስምምነት መሠረት ለደንበኞች የዲጂታል ማይክሮ ብድር አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ማሻሻያዎችን እና ትስስሮችን በማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለና በላቀ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማከል ወደ ደንበኞቹ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
አክለውም አጋርነቱ የአዋሽ ባንክን የፋይናንስ ጥንካሬ እና እምነት ከኤም-ፔሳ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና የሞባይል ገንዘብ አመራር ስርዓት ጋር በማገናኘት በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ድጂታል ብድር ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል። የዚህ ዲጂታል ማይክሮ ብድር ተጠቃሚዎች በቀላሉ በእጅ ስልኮቻቸው ፈጣን አገልግሎት ወዲያውኑ እንደሚያገኙ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አክለው ተናግረዋል።
የM-PESA ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤልሳ ሙዞሊኒ በበኩላቸው ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ምሰሶ ከሆነው አዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር የደንበኞቻችንን የፋይናንስ ደህንነት ለማሻሻል ያለው ዕድል ከፍተኛ ነው ያሉ ሲሆን ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የምንችለው እንደ አዋሽ ባንክ ካሉ ተቋማት ጋር በጠንካራ አጋርነት በመስራት ብቻ ነው ብለዋል ።
የመጀመሪያ የዲጅታል ክሬዲት ምርታችን በሆነው እርፍ በኤም-PESA፣ ደንበኞቻችን የብድር ግብይትን ለማስፋፋት ብቻ ሳይሆን የደንበኞቻችንን ቁጥር ለመጨመር የሚያስችል ትልቅ ዕድል መሆኑ ተገልጿል።



















