የማህበራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት የሚታወቀው አዋሽ ባንክ ስራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታትና ተገቢውን የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ሲያካሄድ የነበረውን የ2ኛው ዙር የ“የቀጠሌዋን” የስራ ፈጠራ ውድድር የማጠቃለያ መርኃ-ግብር በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በድምቀት አካሄዷል፡፡
በፕሮጀክቱ ላይ በርካታ ወጣቶች በመሳተፍ የቢዝነስ ሙያ ስልጠና ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ለተከታታይ ሳምንታት ሰፊ የቴሌቪዥን የስርጭት ሽፋን በነበረው የስራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ላይም በናሙና (prototype) የተደገፈ ስራዎቻቸውን በማቅረብና ብርቱ ፉክክር በማድረግ በዳኞች ውሳኔ መሰረት ከ 1–5ኛ ደረጃ ለወጡ ተወዳዳሪዎች ከ200 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በተጨማሪም ፕሮጀክታቸውን እውን የሚያደርጉበት እስከ ብር 5 ሚሊዮን ብድር ያለዋስትና እንደየ ፕሮጀክታቸው ሁኔታ ይመቻችላቸዋል፡፡
ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው እንደገለፁት የባንኩ የኮርፖሬት ማህበራዊ ሃላፊነት አካል የሆነው የቀጠሌዋን ፕሮጀክት ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ይህ የስራ ፈጠራ ውድድር ከሀሳብ ማመንጨት ጀምሮ እስከ ፕሮግራሙ ፍፃሜ ድረስ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የ2ኛው ዙር የቀጠሌዋን የሥራ ፈጠራ ውድድር ተሸላሚዎችን ይፋ የማድረጊያ መርሐ-ግብር በመጪው እሁድ የካቲት 02 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ በ OBN ቴሌቪዥን ይመልከቱ ከወዲሁ እንጋብዛለን።



















