አቶ ለይኩን ብርሃኑ ገምታ ከአባታቸው ከአቶ ብርሃኑ ገምታ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጉደቱ አንበቻ ሰኔ 4 ቀን 1937 ዓ.ም በቀድሞ ወለጋ ክፍለ ሀገር በጊምቢ አውራጃ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በጊምቢ ደጅአዝማች ገ/እግዚአብሔር አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የመጀመሪያ
ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቀድሞ አጠራርነቀምቴ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ከዚያምበመቀጠል የከፍተኛ ትምህርታቸውን በቀድሞ አጠራር ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሐምሌ ወር 1961 ዓ.ም. በከፍተኛ ውጤትአጠናቀው በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የመጀመሪያ
ድግሪያቸውን ተቀብለዋል።
አቶ ለይኩን ብርሃኑ በሕይወት ዘመናቸው በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ለ47 ዓመታት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶችአገራቸውንና ሕዝባቸውን አገልግለዋል፡፡ ከጥር 1968 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 1971 ዓ.ም. የቀድሞ የአዲስ ባንክ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከጥቅምት 1971 ዓ.ም. እስከ 1972 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም ለባንኪንግ ኢንዱስትሪው እድገት ላደረጉት በጐ ተጽእኖ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማኔጅመንት
ሚያዝያ 7 ቀን 2011ዓ.ም. በስማቸው ‘’ለይኩን ብርሃኑ’’ቅርንጫፍ ከፍቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ ከጥቅምት 1972 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 1975 ዓ.ም. የእርሻ
ሰብል ገበያ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመጋቢት 1978 ዓ.ም. እስከመስከረም 1981 ዓ.ም. የትራንስፖርትና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ዋና ኃላፊ እንዲሁም ከጥቅምት 1982 እስከ ጥቅምት 1984 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ኃላፊነታቸውን በብቃት ተወጥተዋል፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ በ1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥትን መውደቅ ተከትሎ አገራችንኢትዮጵያ የተከተለችውን የኢኮኖሚክ ሪፎርም ኘሮግራም ከህዳር 1984 ዓ.ም. እስከ መስከረም 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን በአስተባባሪነትና በአስፈጻሚነት ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በተለይም በደርግ ዘመነ መንግሥት ለ17 ዓመታት ለግሉ ዘርፍ ዝግ ሆኖ የቆየውን የባንክና የኢንሹራንስ ዘርፍ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ክፍት ለማድረግ አዳዲስ ባንኮችና ኢንሹራንሶች እንዲቋቋሙ የባንክና ኢንሹራንስ ሥራ ፈቃድ አዋጆችን በማውጣት በአሁኑ ጊዜ 30 የግል ባንኮች እና 17 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲቋቋሙ መንገድ የከፈቱና የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡ ባለራዕይና አስተዋይ መሪ ነበሩ፡፡
አቶ ለይኩን ብርሃኑ የኢትÄጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በነበሩበት ጊዜ በኢትÄጵያ ላይ ተቆልሎ የነበረው የውጭ ዕዳ ጫና በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ፣ እንዲሁም አብዛኛው ደግሞ እንዲሰረዝ ከአበዳሪ ድርጅቶች ጋር በመደራደር አመርቂ ውጤትያስመዘገቡ ጠንካራ መሪ ነበሩ፡፡ አቶ ለይኩን ብርሃኑ በመጨረሻው የሥራ ዘመናቸው ከመጋቢት 1988 ዓ.ም. እስከ ታህሣስ 2003 ዓ.ም. የአዋሽ ባንክ አክሲÄን ማህበር ኘሬዚዳንት በመሆን ባንኩን ከ14 ዓመታት በላይ በኘሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡በዚህ ጊዜ ውስጥ ባንኩን እንደ ልጃቸው በመመልከት ሙሉ እውቀታቸውንና ጊዜያቸውን ሣይቆጥቡ ባንኩ ዛሬ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ ጠንካራ መሠረት የጣሉና የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ የባንኩ ባለውለታና ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አዋሽ ባንክ እና አዋሽ ኢንሹራንስኩባንያ በጋራ ያስገነቡትን የዋና መ/ቤት ሕንፃ በማስጨረስና ለአገልግሎት በማብቃት በግል ባንኮችና ኢንሹራንሶች ዘንድ ፈር ቀዳጅ እና ታሪካዊ የሆነ ሥራ ሰርተዋል፡፡ አቶ ለይኩን ብርሃኑ በሙያቸው እና በእውቀታቸው ሙያዊ ምክርና አመራር በመስጠት የተለያዩድርጅቶችንና ማህበራትን አገልግለዋል፡፡ የኢትÄጵያ ባንኮች ማህበር መሥራችና ሊቀመንበር፣ የኢትÄጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ብሔራዊ ኮሚቴ አባል፣ የአዋሽ ባንክና የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል፣ የ “PSS” መሥራች አባል በመሆን በተለያዩ ጊዜያቶች አገልግለዋል፡፡ አቶ ለይኩን ዕድሜያቸው ለጡረታ ደርሶ በጡረታ ከተገለሉ በኋላም ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ ልምዳቸውንእና የህይወት ተሞክሯቸውን ለሌሎች በማጋራት ሀገራቸውን በታማኝነት በማገልገል ለሌሎች መልካም አርአያ የሆኑ የሀገር ባለውለታ ነበሩ። አቶ ለይኩን ብርሃኑ በተፈጥሮአቸው ሩቅ አሳቢ፣ በአቋም ጽናታቸው የሚታወቁ፣ ሥራ ወዳድ እና ጉምቱ የባንክ ባለሙያ ነበሩ፡፡ አቶ ለይኩን ብርሃኑ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸውግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
አቶ ለይኩን ብርሃኑ ከወ/ሮ ስሉስ አስፋው ኃይሌ ጋር ሚያዝያ 1960 ዓ.ም.
የተጋቡ ሲሆን ሦስት ወንድ ልጆችእና ስድስት ሴት ልጆች ወልደዋል፡፡ እንዲሁም የአስራ ሰባት የልጅ ልጆች አያት መሆን የቻሉ ሲሆን፣ የአንድ የልጅ ልጅ ቅድመአያት ነበሩ። ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለሙያ አጋሮቻቸው ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።
ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአጸደ ገነት ያሳርፍልን!
ግንቦት 6፣2017 ዓ.ም

















