አዋሽ ባንክ የነዳጅ ግብይትን በአዋሽብር ፕሮ ዲጂታል የነዳጅ ክፍያ መተግበሪያ ለመክፈል የሚያስችል አዲስ የዲጅታል ክፍያ ስርዓትን በይፋ አስጀመረ
——–
(አዋሽ ባንክ፣ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም)
በቴክኖሎጂ የተደገፈ እና ዘመኑን የዋጀ የባንክ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለማቅረብ ሁሌ የሚተጋው አዋሽ ባንክ በዛሬው እለት የነዳጅ ግብይትን በአዋሽብር ፕሮ መተግበሪያ በቀላሉ ለመክፈል የሚያስችል አዲስ የዲጅታል ክፍያ ስርዓትን በይፋ አስጀመሯል።
አዋሽ ባንክ የዲጂታል ነዳጅ ግብይቱን ተደራሽነት ለማስፋት በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አማካኝነት በበለጸገዉ የተማከለ የነዳጅ መተግበሪያ (Fuel Aggregator System) ላይ የባንኩን አዋሽብር ፕሮ ዲጂታል መተግበሪያን በማናበብ በቀላሉ የነዳጅ ክፍያ መፈጸም የሚያስችል አሰራር መሆኑ ተጠቁሟል።
የክፍያ መተግበሪያው አጠቃቀም የባንኩ ደንበኞች በየትኛውም ስፍራ ሆነው የነዳጅ ፍጆታ ክፍያዎቻቸውን በአዋሽ ብር-ፕሮ(Awashbirr-pro) የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ በመጠቀም በኪው-አር ኮድ (QR code) እንዲሁም የደንበኛውን ስልክ በመጠቀም በዩኤስኤስ.ዲ (USSD) የደንበኛውን የይለፍ ቃል በማስገባት ብቻ ክፍያ መፈጸም የሚያስችል ነው።
አዲስ አበባ ራስ ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የነዳጅ ማደያ በመገኘት አዲሱን የነዳጅ ግብይት ክፍያ አሰራር በይፋ ያስጀመሩት የአዋሽ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉሬ ኩምሳ፣ የባንኩ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደሰ ገመዳ እና የትራንስፕረትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ሰልማን መሐመድ ናቸው።



















