አዋሽ ባንክ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በአጋርነት ጥላ የተሰኘ አነስተኛ የብድርና የቁጠባ አገልግሎቶችን እንዲሁም የዲቫይስ ፋይናንሲግ አገልግሎቶች በቴሌብር አማካኝነት ማስጀመሩን ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው!
በዛሬው እለት በአጋርነት የተጀመረው ይህ አገልግሎት ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣንና ቀላል በሆነ አማራጭ ዲጂታል የአነስተኛ ቁጠባ እና ብድር አገልግሎት የሚያስገኝ ነው። በተጨማሪም በተመጣጣኝ ዋጋ እና በረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጮች የስማርት ዲቫይስ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ያካትታል።
ይህን አገልግሎት ልዩ የሚያደርገው በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ደንበኞች ተያዥ ሳያስፈልጋቸው ያለዋስትና (non-Collateral) የቴሌብር እና የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ተጠቃሚ በመሆናቸው ብቻ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በሚታገዝ የብድር ቀመር ስሌት (Credit Score) የብድር አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል መሆኑ ነው።
ጥላ የዲጂታል የብድር አገልግሎት የ15 ቀን፣ የ40 ቀን እና የ75 ቀን የብድር አማራጮችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከ5,000 ብር ጀምሮ እስከ 16,000ብር የሚደርስ የገንዘብ መጠን ለደንበኞች ማቅረብ ያስችላል::
እንዲሁም የአዋሽ ባንክ እና የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞችን ጨምሮ ወርሃዊ ደመወዛቸው በቴሌብር እና በአዋሽ ባንክ ለሚከፈላቸው የግል እና የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች በ16 ወራት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የስድስት ወር ደመወዝ ክፍያ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ብድር እንዲያገኙ የሚያስችል አማራጭን ያካተተ መሆኑን በዚህ የማስጀመሪያ ስነ-ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር አገልግሎቱ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች፣ ነጋዴዎችና ወኪሎች አነስተኛ ንግድ/ቢዝነስ እንዲጀምሩ ወይም እንዲያስፋፉና ተጨማሪ የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ያስችላል፡፡ በዚህም መሰረት እነዚህ አካላት በቴሌብር እና በአዋሽ ባንክ ሞባይል ባንኪንግ በሚያደርጉት የግብይት መጠን ላይ ተመስርቶ ከብር 50,000 እስከ 150,000 የሚደርስ በአንድ፣በሶስት እና በስድስት ወር የሚከፈል ብድር ተመቻችቷል፡፡ ለእነዚህም የብድር አገልግሎቶች በዓመት በጠቅላላው እንደ መነሻ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ የሚደርስ የብድር አቅርቦት መጠን ስምምነት ተደርጓል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮ ቴሌኮም ከአዋሽ ባንክ ጋር በዓመት ከ3.58 ሚሊየን በላይ የሚደርሱ የስማርት ስልኮችን በተለያዩ የረጅም ጊዜ የክፍያ አማራጮች ለዜጎች ለማቅረብ የዲቫይስ ፋይናንሲንግ ስምምነት ላይ በመድረስ ተግባራዊ ተደርጓል። አገልግሎቱ በተለይም በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ጨምሮ፣ ሰራተኞች፣ ነጋዴዎችና ወኪሎች የተለያዩ የቴሌኮም መገልገያ መሳሪያዎችን (devices) በረጅም ጊዜ ክፍያ (installment) ከሲም ካርድ ጋር እንዲያገኙ ያስችላል።
በተጨማሪም በዛሬዉ ዕለት በይፋ በተጀመረው አገልግሎት ደንበኞች ቴሌብርን ብቻ ተጠቅመው ከአዋሽ ባንክ ኤቲኤም (ATM) ማሽኖች ገንዝብ ማውጣት የሚችሉበት፣ እንዲሁም በቴሌብር ሱፐርአፕ አዋሽ ባንክ ስኩል ፔይን በማካተት የትምህርት ቤት ክፍያዎችን ለማከናወን የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ተገልጿል።
አዋሽ ባንክ!



















