አዋሽ ባንክ አክሲዮኖቹን በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዋዕለ ንዋዮች ገበያ (ESX) ላይ በይፋ መገበያየት ጀመረ፡፡

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2018 (አዋሽ ባንክ) 
በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዉስጥ  የበኩሉን  አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኘው አዋሽ ባንክ፣አክሲዮኖቹን በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ (ESX) ዋና የግብይት መድረክ ላይ በይፋ
መገበያየት መጀመሩን ዛሬ ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ ዋና መስሪያ ቤት በተደረገዉ  ይፋዊ የደወል መደወል (Bell Ringing Ceremony) ስነ-ሥርዓት ላይ አስታውቋል፡፡  
ባንኩ ከ54 ሚሊዮን በላይ አክሲዮኖችን ወደ ካፒታል ገበያ ማስገባቱን እና በባንኩም ሆነ በባለ አክሲዮኖች ዘንድ ትልቅ ክስተት እና ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጸሐይ ሽፈራዉ  በዚሁ የማብሰሪያ ስነስርዓት ላይ  ተናግረዋል፡፡ ይህም ሁኔታ ባለአክሲዮኖች በቀላሉ አክሲዮኖቻቸውን ወደ ጥሬ ገንዘብ እንዲቀይሩ በማስቻል የገበያ ንቁነትን (Liquidity) የሚያሳድግ እና ለአገራችን የፋይናንስ የወደፊት ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ  የሚያድርግ  መሆኑን አቶ ጸሐይ ሽፈራዉ አክለዉ ገልጸዋል።
አዋሽ ባንክ ሁልጊዜም በዘርፉ ቀዳሚ ሆኖ እንደቆየው ሁሉ፣ ዛሬም በገበያው ላይ ከተመዘገቡ ቀዳሚ ተቋማት አንዱ በመሆን ታሪኩን አድሷል። ይህ ምዝገባ ባንኩ በፈጠራ እና ለትውልድ በሚተርፍ የእሴት ግንባታ ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲቀጥል ያስችለዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፣ አዋሽ ባንክ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ከሚጠበቅበት ከፍተኛ የአሰተዳዳርና የግልጽነት ሪፖሪት አቀራረብ ጋር ለመጣጣም በርካታ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ ባንኩ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች ቀጣይነት ባለዉ መልኩ እንዲተገበሩ የውስጥ ፖሊሲና የአሰራር ማዕቀፎችን የዘረጋ ሲሆን በተጨማሪም የአስተዳዳር ማሻሻዎችን አድርጓል፡፡
ምዝገባው የግሉ ዘርፍ  የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ማዕከላዊ ሚና መጫወት እንዲችል  ለሴክተሩ ተሳትፎ እና  መነሳሳት መልዕክት ያስተላልፋል።
አዋሽ ባንክ የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያን  በመቀላቀል ለላቀ ተቋማዊ አስተዳደር፣ ግልጽነት እና ለባለአክሲዮኖች ተጠያቂነት ያለውን ጽኑ አቋም ዳግም ያረጋገጠ  ሲሆን ፣  ከዛሬ ጀምሮ ነባር እና አዲስ ባለአክሲዮኖች የባንኩን አክሲዮኖች  ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ደህንነቱ በተጠበቀ የግብይት ስርዓት ውስጥ መገበያየት የሚችሉ መሆኑን አስታዉቋል።

Loading exchange rates...