አዋሽ ባንክ ሦስት አዳዲስ መተግበሪያዎችን ይፋ አደረገ

 
አዋሽ ባንክ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ አልሞ የጀመረውን ጉዞ በማጠናከር፣ ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስካይላይት ሆቴል ባከናወነው ደማቅ ስነ-ስርዓት ሦስት አዳዲስ ዲጂታል መተግበሪያዎችን በይፋ ስራ አስጀምሯል። ባንኩ በዛሬው ዕለት ስራ ያስጀመራቸው እነዚህ መተግበሪያዎች አዋሽ ሬሚት፣ አዋሽ ኢ-ቲኬቲንግ እና አዋሽ ኢ-ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት የተሰኙ ሲሆኑ፣ በባንክ አገልግሎት ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍቱ ታምኖባቸዋል።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ አዋሽ ባንክ ላለፉት ዓመታት የዲጂታል መሠረተ-ልማቶችን በስፋት ሲገነባ መቆየቱን አስታውሰዋል። ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም፣ ባንኩ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ የዲጂታል አማራጮችን በማቅረብ ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑንና የዛሬው ምርቃትም የዚሁ ቀጣይነት ያለው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በይፋ ስራ ከጀመሩት አገልግሎቶች መካከል ቀዳሚው አዋሽ ሬሚት ሲሆን፣ መተግበሪያው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቪዛ (Visa) ወይም የማስተር ካርድ (MasterCard) አማራጮችን በመጠቀም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በቀጥታ ወደ አዋሽ ባንክ ሂሳብ ወይም ወደ “አዋሽ ብር ፕሮ” ዋሌት ፈጣን እና ደህንነቱ የተጠበቀ የገንዘብ ዝውውር እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። ይህም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎች ያለ እንግልት ገንዘብ እንዲልኩ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው።
ሁለተኛው መተግበሪያ አዋሽ ኢ-ቲኬቲንግ ደግሞ ኮንሰርቶችን፣ ስፖርታዊ ውድድሮችን፣ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎችን እና መሰል ኩነቶችን የሚያዘጋጁ አካላት ትኬቶችን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መንገድ እንዲሸጡና እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል ነው። ይህ አገልግሎት የወረቀት ትኬቶችን በዘመናዊ የQR Code በማስቀረት ለታዳሚዎች ምቾትን፣ ለአዘጋጆች ደግሞ ግልጽና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የሽያጭ ቁጥጥርን የሚያበረክት ነው።
በተጨማሪም ባንኩ ይፋ ያደረገው አዋሽ ኢ-ፕሮፐርቲ ማኔጅመንት ሲስተም የሕንፃ ባለቤቶችንና ተከራዮችን የዕለት ተዕለት ግንኙነት ለማቅለል የተዘጋጀ ነው። መተግበሪያው የህንፃ ኪራይ አስተዳደርን፣ የፋይናንስ ክትትልን፣ የወለል ፕላኖችን እና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ በዲጂታል መንገድ ለመምራት የሚያስችል ሲሆን፣ በተለምዶ የሚሰራውን በእጅ የተደገፈ የኪራይ አያያዝ ወደ ዘመናዊና ግልጽ አሰራር እንደሚቀይረው በምርቃቱ ወቅት ተገልጿል።
 

[rates_widgest title="EXCHANGE Rate" selected_currencies="USD, GBP, EUR, AED, SAR, CNY,JPY,CHF" more_link="#"]