አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. የ2025/26 የሂሳብ ዓመት የስራ አፈጻጸምን ለመገምገም እና በቀጣዩ የሥራ ዘመን ዕቅድና ስትራቴጂ ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሥራ አመራር አባላትን ያሳተፈ ዓመታዊ ጉባኤውን በስካይ ላይት ሆቴል እያካሄደ ይገኛል ።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አዋሽ ባንክ በ2025/26 የሂሳብ ዓመት የላቀ የሥራ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከግል ባንኮች መካከል የመሪነት ቦታውን በተጨባጭ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በሂሳብ ዓመቱም ባንኩ ከ1.8 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር በዲጅታል ክፍያ አማራጮች ማከናወኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዲጂታል የብድር መተግበሪያ ከ 2.7 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠት መቻሉን እና በሂሳብ ዓመቱ 40.7 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡ይህም በባንኩ ታሪክ አዲስ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ውጤት የደንበኞቻችንን እምነት፣ የሠራተኞቻችንን ትጋት እና የባለድርሻ አካላትን ትብብር የሚያሳይ መሆኑን እና በቀጣይም በፈጠራ፣ በዲጂታል ልማት እና በአገልግሎት ጥራት ላይ በማተኮር የበለጠ እሴት ለደንበኞች ለማቅረብ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
አዋሽ ባንክ በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል ባንኪንግ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት በማድረግ ዘመናዊ የኮር ባንኪንግ ሥርዓት፣ የሥራ ሂደት አውቶሜሽን፣ የዳታ ሴንተር ግንባታ እና የሳይበር ደህንነት ማጠናከሪያ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እያከናወነ ይገኛል። ይህም ባንኩን ለወደፊቱ ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያዘጋጅ መሠረት እንደሆነ ተገልጿል ።
በፋይናንስ አፈጻጸምም የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ፣ ጠቅላላ ሀብት፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ የዲጂታል ግብይቶች እና የትርፍ መጠን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ታሪካዊ ውጤት ተመዝግቧል። ይህ አፈጻጸም የባንኩን ጠንካራ የፋይናንስ አቅም፣ የደንበኞች መተማመን እና ዘላቂ ዕድገትን በግልጽ ያረጋግጣል።
የአዋሽ ባንክ ስኬት በዓለም አቀፍ ዕውቅናም ጭምር ተረጋግጧል። ባንኩ በGlobal Finance መጽሔት “The Best Bank in Ethiopia 2025” በመባል ለአምስተኛ ተከታታይ ዓመት ተሸላሚ ሆኗል። ይህ ክብር የአዋሽ ባንክ በፈጠራ፣ በአገልግሎት ጥራት እና በደንበኛ ተኮር አሠራር ያለውን የላቀ አቅም የሚያረጋግጥ ነው።
ጉባኤው በነገው እለትም የሚቀጥል ሲሆን ቀጣይ የስራ እቅድ እና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡



















