በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሶስት አስርት ዓመታትን በቀዳሚነት ወደ ገበያ በመግባት የሚጠቀሱት አዋሽ ባንክ እና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ-ግብር በዛሬው እለት ማለትም ጥር 01 ቀን 2017 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የፋይናንስ ተቋማቱን የ30 ዓመታት ጉዞ በተመለከተ የሁለቱም ተቋማት ሥራ አስፈጻሚዎች በዛሬው እለት ማለትም ጥር 01 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በገበያ ውስጥ የያዙት ድርሻ እየሰፋ መምጣቱንም ጠቁመው በተለይ በኢንዱስትሪው ውስጥ በየዘርፋቸው በገበያው ውስጥ በመሪነት ደረጃ የሚያስቀምጣቸውን አፈጻጸም ማስቀጠላቸውንና ለዚህም ስኬት እንዲበቁ ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ደንበኞች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በ30 ዓመታት ጉዞ እህት ኩባንያዎቹ በተከታታይ ስኬትን በማስመዝገብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የባንክና የኢንሹራንስ የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ በማድረግ ገቢያቸውን በማሳደግና በትርፋማነት በመጓዝ ለአገራዊ ኢኮኖሚው የበኩላቸውን አበርክቶ እየሰጡ መሆኑንም ሥራ አስፈጻሚዎች በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ በሚገኘው የኩባንያዎቹ የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሐ-ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሀላፊዎች፣ የሁለቱም ተቋማት ደንበኞችና በርካታ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡


















